Joshua 10

ፀሓይ ቆመች

1የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ኢያሱ ጋይን ይዞ እንደ ደመሰሳት
የዕብራይስጡ ቃል በዚህም ሆነ በቍጥር 28፡35፡37፡39 እና 40 ላይ ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ነው።
፣ እንደዚሁም በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በጋይና በንጉሥዋ ላይ ማድረጉን፣ የገባዖን ሰዎችም ከእስራኤል ጋር የሰላም ውል አድርገው በአጠገባቸው መኖራቸውን ሰማ።
2በዚህም እርሱና ሕዝቡ ደነገጡ፤ ምክንያቱም ገባዖን እንደ ነገሥታቱ ከተማ ሁሉ ታላቅ ከተማ፣ በስፋቷም ከጋይ የምትበልጥ፣ ሰዎቿም ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ። 3ስለዚህ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ሆሃም ወደ ተባለው የኬብሮን ንጉሥ ጲርአም ወደተባለው የየርሙት ንጉሥ፣ ያፊዓ ወደ ተባለው የለኪሶ ንጉሥና ዳቤር ወደተባለው የዔግሎን ንጉሥ በመላክ፣ 4“ወደዚህ ወጥታችሁ አግዙኝ፤ ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋር ሰላምን መሥርታለችና ገባዖንን እንምታ” አላቸው።

5ከዚያም አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ማለት የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የያርሙት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥና የዔግሎን ንጉሥ ያላቸውን አስተባብረው፣ ሰራዊታቸውንም ሁሉ ይዘው በመውጣት ገባዖንን ወጓት።

6የገባዖንም ሰዎች በጌልገላ ወደ ሰፈረው ወደ ኢያሱ፣ “በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ኀይላቸውን አስተባብረው ተሰልፈውብናል፤ እኛን ባሮችህን አትተወን፤ ርዳን፤ ፈጥነህ በመድረስም አድነን” ሲሉ ላኩበት።

7ስለዚህ ኢያሱ ምርጥ የሆኑትን ተዋጊዎች ሁሉ ጨምሮ ሰራዊቱን በሙሉ ይዞ ከጌልገላ ወጣ። 8እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “አትፍራቸው፤ ሁሉንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻቸዋለሁ፤ አንዳቸውም እንኳ ሊቋቋሙህ አይችሉም” አለው።

9ኢያሱ ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሥ ዐድሮ ድንገት ወረራቸው። 10እግዚአብሔርም የአሞራውያንን ነገሥታት በእስራኤል ፊት አሸበራቸው፤ በገባዖን እጅግ መታቸው፤ ወደ ቤትሖሮን በሚያስወጣውም መንገድ ሽቅብ ተከተላቸው፤ እስከ ዓዜቅና እስከ መቄዳም ድረስ አሳድዶ መታቸው። 11ከቤትሖሮን ወደ ዓዜቃ ቍልቍል በሚወስደው መንገድ ላይ፣ ከእስራኤላውያን ፊት በሚሸሹበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሰማይ ትልልቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ በእስራኤላውያን ሰይፍ ካለቁት ይልቅ በወረደው የበረዶ ድንጋይ ያለቁት በልጠው ተገኙ።

12 እግዚአብሔር አሞራውያንን ለእስራኤል አሳልፎ በሰጠባት ዕለት፣ ኢያሱ እግዚአብሔርን በእስራኤል ፊት እንዲህ አለው፤

“ፀሓይ ሆይ፤ በገባዖን ላይ ቁሚ፤
ጨረቃም ሆይ፤ በኤሎን ሸለቆ ላይ ቀጥ በዪ።”
13ስለዚህ ሕዝቡ ጠላቶቹን እስኪበቀል
ድረስ
ወይም ሕዝቡ እስኪያሸንፍ ድረስ
፣ ፀሓይ ባለችበት ቆመች፤
ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም።
ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል።

ፀሓይ በሰማዩ መካከል ቆመች፤ ለመጥለቅም ሙሉ ቀን ፈጀባት።
14እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ዕለት ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አልነበረም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ተዋግቶ ነበርና።

15ከዚያም ኢያሱ ከመላው እስራኤል ጋር ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሰ።

አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ተገደሉ

16በዚህ ጊዜ አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተደብቀው ነበር። 17ኢያሱም አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸውን ሰማ፤ 18እንዲህም አለ፤ “ትልልቅ ድንጋዮች ወደ ዋሻው አፍ አንከባሉ፤ ጠባቂ ሰዎችንም በዚያ አቁሙ፤ 19ጠላቶቻችሁን አሳድዷቸው እንጂ ችላ አትበሉ፤ ከበስተ ኋላ ሆናችሁም አደጋ ጣሉባቸው፤ ወደ ከተሞቻቸው እንዳይገቡ ከልክሏቸው፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና።”

20ስለዚህ ኢያሱና እስራኤላውያን እስከ መጨረሻው ደመሰሷቸው፤ የተረፉት ጥቂቶቹ ግን ወደ ተመሸጉት ከተሞቻቸው ለመድረስ ቻሉ። 21ከዚያም ሰራዊቱ ሁሉ በደኅና ተመልሶ፣ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ መጣ፤ በእስራኤላውያንም ላይ አንዲት ቃል የተናገረ ሰው አልነበረም።

22ኢያሱም፤ “ዋሻውን ከፍታችሁ እነዚያን አምስቱን ነገሥታት አውጥታችሁ አምጡልኝ” አላቸው። 23እነርሱም አምስቱን ነገሥታት ማለትም የኢየሩሳሌምን ንጉሥ፣ የኬብሮንን ንጉሥ፣ የያርሙትን ንጉሥ፣ የለኪሶን ንጉሥ የዔግሎንን ንጉሥ አውጥተው አመጡለት። 24እነዚህን ነገሥታት ባመጡለትም ጊዜ፣ ኢያሱ መላውን የእስራኤልን ወንዶች ከጠራ በኋላ አብረውት የመጡትን የጦር አዛዦች፣ “ወደዚህ ቅረቡና እግሮቻችሁን በእነዚህ ነገሥታት ዐንገት ላይ አድርጉ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ፊት ቀርበው እግራቸውን በነገሥታቱ ዐንገት ላይ አሳረፉ።

25ኢያሱም፣ “አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በርቱ፤ ጽኑ፤ እንግዲህ በምትወጓቸው ጠላቶች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር እንደዚሁ ያደርጋልና” አላቸው። 26ከዚያም ኢያሱ ነገሥታቱን መትቶ ገደላቸው፤ በአምስትም ዛፎች ላይ ሰቀላቸው፤ ሬሳቸውም እስኪመሽ ድረስ አልወረደም ነበር።

27ፀሓይ ለመጥለቅ በማዘቅዘቅ ላይ ሳለች ኢያሱ ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም የነገሥታቱን ሬሳ ከዛፎቹ ላይ አውርደው ቀድሞ ተደብቀው ወደ ነበሩበት ዋሻ ውስጥ ጣሏቸው። በዋሻውም አፍ ትልልቅ ድንጋዮች አኖሩ፤ ድንጋዮቹም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይገኛሉ።

28በዚያች ዕለት ኢያሱ መቄዳን ያዘ፤ ከተማዪቱንና ንጉሥዋንም በሰይፍ ስለት መታ፤ አንድም ሰው ሳያስቀር በውስጧ ያለውን ሁሉ ፈጽሞ ደመሰሰ፤ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ ያደረገውንም ሁሉ፣ በመቄዳ ንጉሥ ላይ አደረገ።

የደቡብ ከተሞች መያዝ

29ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከመቄዳ ወደ ልብና ዐለፉ፤ ወጓትም። 30እንዲሁም እግዚአብሔር ከተማዪቱንና ንጉሥዋን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። ኢያሱ ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ በሰይፍ ስለት አጠፋ፤ አንድም ሰው አላስተረፈም። በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ ያደረገውንም በልብና ንጉሥ ላይ ደገመው።

31ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከልብና ወደ ለኪሶ ዐለፉ፤ ወጓትም። 32እግዚአብሔር ለኪሶን አሳልፎ ለእስራኤል ሰጠ፤ ኢያሱም በሁለተኛው ቀን ያዛት፤ በልብና እንዳደረገው ሁሉ እዚህም ከተማዪቱንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጃቸው። 33በዚህ ጊዜ የጌዝር ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት መጣ፤ ኢያሱ ግን አንድ እንኳ ሳያስተርፍ ንጉሡንና ሕዝቡን መታቸው።

34ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከለኪሶ ወደ ዔግሎን ዐለፉ፤ ወጓትም። 35በዚያኑ ዕለት ያዟት፤ በሰይፍም ስለት አጠፏት፤ በለኪሶ እንዳደረጉት ሁሉ እዚህም በውስጧ የሚገኙትን ፈጽመው ደመሰሷቸው።

36ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከዔግሎን ወደ ኬብሮን ወጡ፤ ወጓትም። 37ከተማዪቱንም ከንጉሧ፣ ከመንደሮቿና በውስጧ ካሉት ጋር ሁሉ አንድም ሰው ሳያስቀሩ በሰይፍ ስለት ፈጇቸው፤ በዔግሎን እንዳደረጉት ሁሉ እዚህም ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ ፈጽመው ደመሰሱ።

38ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ኋላ ተመልሰው ዳቤርን ወጓት። 39ከተማዪቱን፣ ንጉሥዋንና መንደሮቿን ይዘው በሰይፍ ስለት ፈጇቸው፤ በውስጧ ያለውንም ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ ደመሰሱ፤ በልብናና በንጉሥዋ እንዲሁም በኬብሮን ያደረጉትን ሁሉ እዚህም በዳቤርና በንጉሥዋ ላይ ደገሙት።

40በዚህ ሁኔታም ኢያሱ ተራራማውን አገር ኔጌቭን፣ የምዕራቡን ቈላና የተራራውን ሸንተረሮች ጨምሮ ምድሪቱን በሙሉ ከነገሥታቷ ጋር ያዘ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት፣ እስትንፋስ ያላቸውን ሁሉ ፈጽሞ ደመሰሰ፤ ማንንም በሕይወት አላስቀረም። 41ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ እንዲሁም የጎሶምን ምድር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ በሙሉ ያዘ። 42ኢያሱ እነዚህን ሁሉ ነገሥታትና ምድራቸውን ያሸነፈው በአንድ ዘመቻ ብቻ ነበር፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ተዋግቶላቸዋልና።

43ከዚህ በኋላ ኢያሱ ከመላው እስራኤላውያን ጋር ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሰ።

Copyright information for AmhNASV